አንደኛ - የአላህንﷻ ተውሒድ እውን በማድረግ። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦
(مُخۡلِصٗا لَّهُ ٱلدِّينَ٢أَلَا لِلَّهِ ٱلدِّينُ ٱلۡخَالِصُ)
‹‹ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ ያጠራህ ኾነህ ተገዛው። ንቁ! ፍጹም ጥሩ የኾነው ሃይማኖት የአላህ ብቻ ነው።››
[አልዙመር፡2-3]
በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦
( وَمَآ أُمِرُوٓاْ إِلَّا لِيَعۡبُدُواْ ٱللَّهَ مُخۡلِصِينَ لَهُ ٱلدِّينَ)
‹‹አላህን ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ አጥሪዎች፣ ቀጥተኞች ኾነው ሊግገዙት፣. . እንጅ ያልታዘዙ ሲኾኑ (ተለያዩ)።››
[አልበይይናህ፡5]
ሁለተኛ - ለአላህ መልክተኛ ﷺ ተከታይ መሆንን በማረጋገጥ፣ያዘዙትን በመፈጸም፣ከከለከሉት ሁሉ በመራቅና የተናገሩት ሁሉ እውነት መሆኑን በመቀበል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦
(يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ أَطِيعُواْ ٱللَّهَ وَأَطِيعُواْ ٱلرَّسُولَ وَأُوْلِي ٱلۡأَمۡرِ مِنكُمۡۖ فَإِن تَنَٰزَعۡتُمۡ فِي شَيۡءٖ فَرُدُّوهُ إِلَى ٱللَّهِ وَٱلرَّسُولِ إِن كُنتُمۡ تُؤۡمِنُونَ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِۚ ذَٰلِكَ خَيۡرٞ وَأَحۡسَنُ تَأۡوِيلًا٥٩)
‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ተገዙ፤መልክተኛውንና ከናንተም የሥልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ፤በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ፣በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትኾኑ (የተከራከራችሁበትን ነገር) ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት፤ይህ የተሻለ፣መጨረሻውም ያማረ ነው።››
[አልኒሳእ፡59]
ሦስተኛ - ሙኽሊስ መሆን ከፈለግህ በመልካም ሥራህ ላይ ትጋት ይኑርህ፤ከርሱ ጥላ በስተቀር ሌላ ጥላ በሌለበት የቅያማ ቀን አላህﷻ በጥላው ስር ከሚያስጠልላቸው ሰባቱ ውስጥ አንዱ፦
‹‹ . . መጽዋትን መስጠቱን የደበቀ (ደብቆ የሰጠ) ሰው . . ›› መሆኑን ሁሌ አስታውስ።
(በቡኻሪ የተዘገበ)
በተጨማሪም ፦
‹‹ሥራዎች (የሚለኩት) በንይ'ያ (ከጀርባቸው ባለው ቁርጠኛ) . . ›› መሆኑን አስታውስ።
(በቡኻሪ የተዘገበ)
አራተኛ - ልብህ የሰውን ምስጋና እና ውዳሴ ወደ መውደድ አያምራ። በሰዎች እጅ ካለው ነገር ሁሉ ተስፋ ቆርጠህ በፈጣሪህ ላይ ብቻ ተስፋህን ጣል። ለጌታው ፍጹም የሆነ ሙኽሊስ ሰው ለሚያገኘው ሀብት ወይም ለሚያገባት ሴት አይጓጓም፤የሚከጅለውና የሚጓጓው ለአላህﷻ እዝነትና ችሮታ ነው።
አምስተኛ - ፍጹምነትንና ቅን ልቦናን ይሰጥህ ዘንድ፣ከልታይባይነት አጥርቶህ ያለፉ ኃጢቶችህን ይምርህ ዘንድ ከጌታህ ፊት ወድቀህ ከደጁ በመንከባለል እርሱን መለመንና መማጸን ይኖርብሃል።
ከአላህﷻ በስተቀር ለሥራህ መስካሪና ሸላሚ ባለመፈለግ ለርሱ ብቻ ፍጹም ሁን።
ስድስተኛ - ከታይታና ከመመጻደቅ መራቅና መጠንቀቅ። አንድ የአላህ አገልጋይ ታይታ (ሪያእ) ወደ ልቡ የሚመጣበትን መንገድና መግቢያ በሩን ካላወቀ፣ከእኽላስ መንገድ ይርቃል። በዚህ ምክንያት ነው አንዳንድ ሰዎች የአላህ ጻድቅ (ወሊይ) አድርገው ራሳቸውን ሲገልጹ የሚስተዋሉት፣ወይም ሌሎች እንደዚያ ተብለው መጠራትን የሚወዱት፣ወይም ስለ ዕባዳቸውና ስለ በጎ ሥራዎቻቸው ማውራትና መመጻደቅን የሚያዘወትሩት።
አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦
(مَن كَانَ يُرِيدُ ٱلۡحَيَوٰةَ ٱلدُّنۡيَا وَزِينَتَهَا نُوَفِّ إِلَيۡهِمۡ أَعۡمَٰلَهُمۡ فِيهَا وَهُمۡ فِيهَا لَا يُبۡخَسُونَ١٥أُوْلَٰٓئِكَ ٱلَّذِينَ لَيۡسَ لَهُمۡ فِي ٱلۡأٓخِرَةِ إِلَّا ٱلنَّارُۖ وَحَبِطَ مَا صَنَعُواْ فِيهَا وَبَٰطِلٞ مَّا كَانُواْ يَعۡمَلُونَ ١٦)
‹‹ቅርቢቱን ሕይወትና ጌጣጌጧን የሚሹ የኾኑትን ሰዎች፣ሥራዎቻቸውን (ምንዳዋን) በርሷ ውስጥ ወደነሱ እንሞላላቸዋለን፤እነርሱም በርሷ ውስጥ ምንም አይጎድልባቸውም። እነዚያ እነርሱ በመጨረሻይቱ ዓለም ለነርሱ ከእሳት በቀር የሌለላቸው ናቸው፤የሠሩትም ሥራ በርሷ ውስጥ ተበላሸ፤(በቅርቢቱ ዓለም) ይሠሩት የነበሩትም በጎ ሥራ ብልሹ ነው።››
[ሁድ፡15-16]
ታይታ ትንሹ ሽርክ (በአላህ ማጋራት) ነው። ከአስከፊ ፍጻሜው መካከል ሥራዎች ላይ ላዩን በጎ ቢመስሉ እንኳ በእኽላስ ካልተሠሩ ተቀባይነት የማይኖራቸውና ወደ ባለቤቶቻቸው የሚመለሱ ወዳቂ መሆናቸው ብቻ በቂ ነው።
ሰባተኛ - እኽላስ ካላቸው ሰዎች ጋር መጎዳኘት። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦
‹‹ሰው በወዳጁ ሃይማኖት ላይ ነው (አርአያነቱን ይከተላል) . . ››
(በትርምዚ የተዘገበ)
እኽላስና ምስጋና እና ውዳሴን መውደድ በአንድ ልብ ውስጥ አብረው አይኖሩም፤ውሃ እሳትን እንደሚያጠፋ አንዱ ሌላውን ያወድማል ያጠፋዋል።
ስምንተኛ - ዕባዳን በድብቅና በስውር ማድረግ። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦
(إِن تُبۡدُواْ ٱلصَّدَقَٰتِ فَنِعِمَّا هِيَۖ وَإِن تُخۡفُوهَا وَتُؤۡتُوهَا ٱلۡفُقَرَآءَ فَهُوَ خَيۡرٞ لَّكُمۡ)
‹‹ምጽዋቶችን ብትገልጹ፣እርሷ ምንኛ መልካም ናት፤ብትደብቋትና ለድኾች ብትሰጧትም፣እርሱ ለናንተ በላጭ ነው።››
[አልበቀራህ፡271]
ዘጠነኛ- የገዛ ራስን በማያቋርጥ ሁኔታ ሁሌ በጥብቅና በጥልቀት መመርመር። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦
(وَٱلَّذِينَ جَٰهَدُواْ فِينَا لَنَهۡدِيَنَّهُمۡ سُبُلَنَا)
‹‹እነዚያም በኛ መንገድ የታገሉ፣መንገዳችንን በእርግጥ እንመራቸዋለን፤››
[አልዐንከቡት፡69]
የሚከተለውን የአላህﷻ ቃል አስተውል፦
(فِينَا)!!‹‹በኛ መንገድ››!!
ዐስረኛ - አዘውትሮ ወደ አላህ መጸለይና ፊትን ወርሱ መመለስ። ደሃውና ጎስቋላው ሰው የቸር ጌታውን ደጃፍ ካዘወተረ ይራራለታል፣ያዘንለታል፤የለመነውን ይሰጠዋል፤ችግሩን ይፈታለታል፤የጎደለውንም ያሟላለታል። . . የሚለመነውና የሚጠየቀው አላህﷻ ብቻ ነውና።