የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያቱን መረዳትን የሚመለከቱ መርሆዎችና ማሳሰቢያዎች ፦

የአላህንﷻ  ስሞችና ባሕርያቱን መረዳትን የሚመለከቱ መርሆዎችና ማሳሰቢያዎች ፦
(لَيۡسَ كَمِثۡلِهِۦ شَيۡءٞۖ وَهُوَ ٱلسَّمِيعُ ٱلۡبَصِيرُ١١)

‹‹የሚመስለው ምንም ነገር የለም፤እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው።›› [አልሹራ፡11]

1

- ሁሉም የአላህﷻ ስሞች መልካሞች ናቸው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَلِلَّهِ ٱلۡأَسۡمَآءُ ٱلۡحُسۡنَىٰ)

‹‹ለአላህም መልካም ስሞች አሉት፤››

[አልአዕራፍ፡180]

አላህﷻ የላቀና የተቀደሰ እርሱነቱን (ዛቱን) እንድናውቅ ያደረገን፣እንድናልቀው፣እንድናፈቅረው፣እንድንፈራውና በርሱ ላይ ተስፋችንን እንድንጥል ነው።

2

- የአላህﷻ ስሞች ምንጫቸው ሁለት ብቻ ሲሆን፣እነሱም የአላህﷻ መጸሐፍና የነቢዩ ﷺ ሱንና ናቸው። ከነዚህ ውጭ ሌላ ምንጭ የላቸውም። የአላህﷻ ስሞችና ባሕርያቱ ከሁለቱ ውጭ ሊጸኑ አይችሉም። ስለዚህም አላህﷻ እና ረሱል ﷺ ያጸኑትን አጽንተን እንቀበላለን፤አላህﷻ እና ረሱል ﷺ ያስተባበሉትን አስተባብለን ተቃራኒውን እናጸናለን። የጸና ወይም የተስተባበለ መሆኑ ያልተገለጸውን በተመለከተ፣ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ያልቀረበበት በመሆኑ ጥሬ ቃሉን ከመቀበል እንቆጠባለን። ፍችና ይዘቱን ግን በዝርዝር ተለይቶ ይወሰዳል። ለአላህﷻ ተገቢ በሆነ እውነታ ላይ እንዲያነጣጥር የታለመ ከሆነ ተቀባይነት ይኖረዋል። ለአላህﷻ ተገቢ ያልሆነ ይዘትና ትርጉም ካለው ግን ውድቅ ማድረግ ግዴታ ይሆናል።

3

- የአላህንﷻ ባህርያት አስመልክቶ የሚወሰደው አቋም እርሱነቱን (ዛቱን) አስመልክቶ ከሚወሰደው አቋም ጋር ተመሳሳይ ነው። የተቀደሰ እርሱነቱን አኳኋን እንደማናውቀው ሁሉ፣የላቁ ባሕርያቱን አኳኋንም አናውቅም። ይሁን እንጂ ማዛባት፣ትርጉም የለሽ ማድረግ፣እንዲህ ነው እንደዚያው ነው ብሎ አኳኋን መስጠትም ሆነ ከምንምና ከማንም ጋር ማመሳሰል በሌለበት ሁኔታ ጽኑና ቁርጠኛ የሆነ እምነት አምነን እንቀበላቸዋለን።

4

- የአላህﷻ ስሞችና ባሕርያቱ፣ተምሳሌታዊም እንቆቅልሽም ሳይሆኑ እውነተኛ ትርጉምና ፍች ያላቸው ስሞችና ባሕርያት ናቸው። እንደ የችሎታ ባለቤት፣በጣም ዐዋቂው፣ጥበበኛው፣ሰሚው፣ተመልካቹ የመሳሰሉ የአላህንﷻ እርሱነትና የእርሱነቱን ምሉእ ባሕርያት የሚያመለክቱ ናቸው። እነዚህ ስሞች የአላህንﷻ እርሱነት የሚያመለክቱ ሲሆኑ፣ተግባሩ የሆኑ ፍጹማዊ ችሎታ፣ዕውቀት፣ጥበብ፣ሰሚነትና ተመልካችነቱን ያሳያሉ።

5

- አላህንﷻ ከጉድለቶች ሁሉ ማጥራት የሚገባው ስሞቹንና ባሕርያቱን ትርጉም የለሽ (ተዕጢል) ሳያደርጉ ነው። ጉድለቶችን ከአላህ ማስተባበል በያንዳንዱ ጉድለት ውስጥ የሚጠቃለል ሲሆን፣ምሉእነቱን ማጽናት ደግሞ በያንዳንዱ ባሕሪ ውስጥ የሚዘረዘር ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(لَيۡسَ كَمِثۡلِهِۦ شَيۡءٞۖ وَهُوَ ٱلسَّمِيعُ ٱلۡبَصِيرُ١١)

‹‹የሚመስለው ምንም ነገር የለም፤እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው።››

[አልአንቢያ፡54]

6

- በአላህﷻ ስሞች ማመን በስሙና ስሙ በሚይዘው ባሕሪ ማመንን ግዴታ እንደሚያደርግ ሁሉ፣ከስሙ ጋር በሚተሳሰረውና በውጤቱ ማመንንም ግዴታ ያደርጋል። በጣም አዛኝ (አርረሒም) የሚለው የአላህ ስም አላህﷻ የእዝነት ባሕሪ ያለው መሆኑን በውስጡ ያካተተ በመሆኑ አላህﷻ በእዝነቱ ለባሮቹ ያዝናል።

የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያቱን ለመረዳት የሚያግዙ አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦች ይገኛሉ። እነሱም የሚከተሉት ናቸው ፦

1-

ስሞቹ በቀጥር ተለይተው የተወሰኑ አይደሉም። ሐዲሥ ውስጥ የሚከተለውን እናገኛለን፦

‹‹ . . አንተ ራስህን በሰየምክበት፣ወይም ከፍጥረቶችህ ለአንዱ ባስተማርከው፣ወይም በመጽሐፍህ ውስጥ ባወረድከው፣ወይም በሩቁ ዕውቀትህ አንተ ዘንድ ብቻ ባስቀረኸውና ያንተ በሆነው እያንዳንዱ ስም እለምነሃለሁ . . ››

(በአሕመድ የተዘገበ)

2-

ከአላህﷻ ስሞች መካከል ሌላ ማንም የማይጋራውና ለአንድ አላህ ብቻ የተለዩ፣ከአላህﷻ በስተቀር ማንም ሊጠራባቸው የማይፈቀዱ ስሞች ይገኛሉ። እነዚህም አላህ እና አልረሕማንን የመሳሰሉ ናቸው። ከስሞቹ መካከል ለአላህﷻ ሲሆኑ ስሞቹና ባሕርያቱ ፍጹም ምሉእ ቢሆኑም፣ለሌሎች መጠሪያነት ሊውሉ የሚችሉ ስሞችም ይገኛሉ።

3-

ከአላህﷻ ስሞች ባሕርያት ይመነጫሉ። እያንዳንዱ ስም ባሕሪ (ስፋህ) በውስጡ ያቀፈ ሲሆን፣ከባሕርያት ግን ስሞች አይመነጩም። ‹‹አላህ ይቆጣል›› እንደምንለውና ‹‹አላህ ቁጡው›› ብለን ግን እንደማንገልጸው ማለት ነው። አላህﷻ በቁጡነት ባሕሪ ከመገለጽ የጠራ ነውና።



Tags: