የኢማን ፍሬዎች

የኢማን ፍሬዎች
አላህ ﷻ እንዲህ ይላል፦

(أَلَمۡ تَرَ كَيۡفَ ضَرَبَ ٱللَّهُ مَثَلٗا كَلِمَةٗ طَيِّبَةٗ كَشَجَرَةٖ طَيِّبَةٍ أَصۡلُهَا ثَابِتٞ وَفَرۡعُهَا فِي ٱلسَّمَآءِ ٢٤ تُؤۡتِيٓ أُكُلَهَا كُلَّ حِينِۢ بِإِذۡنِ رَبِّهَا)

‹‹አላህ መልካምን ቃል ሥርዋ (በምድር ውስጥ) የተደላደለች፣ቅርንጫፍዋም ወደ ሰማይ (የረዘመች) እንደ ኾነች መልካም ዛፍ አድርጎ ምሳሌን እንዴት እንደገለጸ አላየኸምን? ምግቧን (ፍሬዋን) በጌታዋ ፍቃድ በየጊዜው ትሰጣለች፤››

[ኢብራሂም፡24-25]

ከኢማን ፍሬዎች መካከል የሚከተሉትን እናገኛለን፦

1-

እውነተኛ ኢማን የመንፈስ እርጋትን የሕሊና ደስታንና የልብ ፍካትን ያጎናጽፋል። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(أَلَا إِنَّ أَوْلِيَاءَ اللَّهِ لَا خَوْفٌ عَلَيْهِمْ وَلَا هُمْ يَحْزَنُونَ)

‹‹ንቁ፣የአላህ ወዳጆች በነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤እነሱም አያዝኑም።››

[ዩኑስ፡62]

2- ከኩፍር ጨለማና ከሚያስከትላቸው አስከፊ ነገሮች ወደ ኢማን ብርሃንና ወደ በረከቶቹ በማውጣት፣አማኞች ከአላህ ﷻ ጋር ልዩ የሆነ አብሮነት እንዲኖራቸው ያደርጋል።

3-

አላህ ﷻ በርሱ አምኖ ላረጋገጠ ሰው ያዘጋጀውን ወዴታውንና ጀነትን ለመታደል ያስችለዋል። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَعَدَ ٱللَّهُ ٱلۡمُؤۡمِنِينَ وَٱلۡمُؤۡمِنَٰتِ جَنَّٰتٖ تَجۡرِي مِن تَحۡتِهَا ٱلۡأَنۡهَٰرُ خَٰلِدِينَ فِيهَا وَمَسَٰكِنَ طَيِّبَةٗ فِي جَنَّٰتِ عَدۡنٖۚ وَرِضۡوَٰنٞ مِّنَ ٱللَّهِ)

‹‹አላህ ምእምናንንና ምእምናትን፣ከስሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች፣በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ፣በመኖሪያ ገነቶችም ውስጥ መልካም መኖሪያ ቤቶችን ቃል ገብቶላቸዋል፤ከአላህም የኾነ ውዴታ ከሁሉ የበለጠ ነው፤››

[አልተውባህ፡72]

4-

አላህ ﷻ ለወዳጆቹ፣ለጭፍራዎቹና ለሚወዳቸው ምእመናን የሚከላከልላቸው መሆኑን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّ ٱللَّهَ يُدَٰفِعُ عَنِ ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ)

‹‹አላህ ከነዚያ ካመኑት ይከላከልላቸዋል፤››

[አልሐጅ፡38]

በዚህ ረገድ በህጅራ ክስተት አላህﷻ ከነቢዩ ሙሐመድ ﷺ የከሐዲዎችን ተንኮል የተከላከለላቸው መሆኑ፣ተወዳጁ ነቢዩ ኢብራሂም  ወደ እሳት በተወረወሩበት ጊዜም የተከላከለላቸው መሆኑ ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።

በአላህ ማመን በደካማው ሰብአዊ ፍጡርና በፈጣሪ ጌታው መካከል የተዘረጋ የግንኙነት መስመር ሲሆን፣ኃይለኛውም ኃይሉን ከርሱ ያገኛል።

5-

በሃይማኖቱ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ መድረስና መሪነትን መቀደጃት። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَجَعَلۡنَا مِنۡهُمۡ أَئِمَّةٗ يَهۡدُونَ بِأَمۡرِنَا لَمَّا صَبَرُواْ)

‹‹በታገሡና በታምራቶቻችን የሚያረጋግጡ በኾኑም ጊዜ፣ከነርሱ በትእዛዛችን የሚመሩ፣መሪዎችን አደረግን፤››

[አልሰጅዳህ፡24]

ለዚህ በአላህ ላይ የጸና እርግጠኝነት የነበራቸውን የእስላም ሊቃውንትና ተግባራውያን ዓሊሞችን፣አላህﷻ ስማቸውንና ዝናቸውን ትውልድ ተሸጋሪ በማድረግ ሁሌም በአርአያነት የሚጠቀሱ፣ከዘመናት በፊት ከዚህ ዓለም ቢለዩና በአካል ባይኖሩም ቅርሳቸው፣ስማቸውና ዝናቸው ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ያደረገላቸው ከመሆኑ የበለጠ ማስረጃ የለም።

6-

አላህ ለምእመናን ያለው ውዴታ። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(يُحِبُّهُمْ وَيُحِبُّونَهُ)

‹‹የሚወዳቸውንና የሚወዱትን።››

[አልማእዳህ፡54]

በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّ ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ وَعَمِلُواْ ٱلصَّٰلِحَٰتِ سَيَجۡعَلُ لَهُمُ ٱلرَّحۡمَٰنُ وُدّٗا ٩٦)

‹‹እነዚያ ያመኑና በጎ ሥራዎችን የሠሩ፣አልረሕማን ለነሱ ውዴታን ይሰጣቸዋል።››

[መርየም፡96]

ያለ ኢማን ሕይወት የተረጋገጠ ሞት ነው . .

ያለ ኢማን ዓይናማነት መታወር ነው . .

ያለ ኢማን አንደበተ ርቱእነት ድዳነት ነው . .

ያለ ኢማን እጅ ሽባነት ነው . .

7-

በሁለቱም ዓለም (በዱንያና በኣኽራ) መልካም ሕይወትን የሚያጎናጽፍ መሆኑ። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(مَنۡ عَمِلَ صَٰلِحٗا مِّن ذَكَرٍ أَوۡ أُنثَىٰ وَهُوَ مُؤۡمِنٞ فَلَنُحۡيِيَنَّهُۥ حَيَوٰةٗ طَيِّبَةٗۖ وَلَنَجۡزِيَنَّهُمۡ أَجۡرَهُم بِأَحۡسَنِ مَا كَانُواْ يَعۡمَلُونَ ٩٧)

‹‹ከወንድ ወይም ከሴት፣እርሱ አማኝ ኾኖ በጎን የሠራ፣መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን።››

[አልነሕል፡97]

ታድያ መልካም ሕይወትና ደስተኝነትን የሚፈልጉ የት ናቸው?!!

8-

አላህ ﷻ አማኙን የሚወድና አማኙም የሚወደው መሆኑ። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(يُحِبُّهُمۡ وَيُحِبُّونَهُۥ)

‹‹የሚወዳቸውንና የሚወዱትን።››

[አልማእዳህ፡54]

ይህም ይወዳቸውና በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነት እንዲኖራቸው ያደርጋል ማለት ነው።

9-

ለኢማን ባለቤቶች አላህ ﷻ ከበሬታ የሰጣቸው መሆኑን ብስራት ይሰጣቸዋል። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَبَشِّرِ ٱلۡمُؤۡمِنِينَ ١١٢)

‹‹ምእምናንንም አብስር።››

[አልተውባህ፡112]

ብስራት ሲነገር በትልቅ ነገር ሲሆን አሻራው በሰውነት ላይ በግልጽ ይስተዋላል። ከአላህ ረሕመትና ከችሮታው፣ከውዴታውና ከጀነቱ የበለጠ ታላቅ ብስራት የለም። አላህ ﷻ እንዲህ ይላል፦

(وَبَشِّرِ ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ وَعَمِلُواْ ٱلصَّٰلِحَٰتِ أَنَّ لَهُمۡ جَنَّٰتٖ تَجۡرِي مِن تَحۡتِهَا ٱلۡأَنۡهَٰرُ)

‹‹እነዚያን ያመኑትንና መልካሞችንም የሠሩትን ለነርሱ ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው ገነቶች ያሏቸው መኾኑን አብስራቸው፤››

[አልበቀራህ፡25]

10-

ኢማን የጽናትና የብርታት መንስኤ ነው። አላህ ﷻ እንዲህ ይላል፦

(ٱلَّذِينَ قَالَ لَهُمُ ٱلنَّاسُ إِنَّ ٱلنَّاسَ قَدۡ جَمَعُواْ لَكُمۡ فَٱخۡشَوۡهُمۡ فَزَادَهُمۡ إِيمَٰنٗا وَقَالُواْ حَسۡبُنَا ٱللَّهُ وَنِعۡمَ ٱلۡوَكِيلُ ١٧٣)

‹‹እነዚያ ሰዎቹ፣ለነርሱ፦ ሰዎች ለናንተ (ጦርን) አከማችተዋልና ፍሩዋቸው ያሏቸውና (ይህም) እምነትን የጨመረላቸው፣በቂያችንም አላህ ነው፣ምን ያምር መጠጊያ! ያሉ ናቸው።››

[ኣል ዒምራን፡173]

ለዚህ ጽናት ከሁሉም የበለጠ ማስረጃ፣በታሪክ የተመዘገበው የነቢያት፣የመልክተኞች፣የሶሓባ፣የነርሱ ተከታዮችና መስመራቸውን ተከትለው የተጓዙት የከፈሉት መስዋእትነት ነው።

11-

በግሣጼና በምክር መጠቀም። አላህ ﷻ እንዲህ ይላል፦

(وَذَكِّرۡ فَإِنَّ ٱلذِّكۡرَىٰ تَنفَعُ ٱلۡمُؤۡمِنِينَ ٥٥)

‹‹ገሥጽም፤ግሣጼ ምእምናንን ትጠቅማለችና።››

[አልዛርያት፡55]

በግሣጼና በምክር የሚጠቀሙት ግን የኢማን ባለቤቶች ብቻ ናቸው።

12-

አማኝ ሰው ሁሉም ሁኔታው ለበጎ እንዲሆን ተደርጓል። በደስታም ይሁን በችግር በጎ ነገር ሁሌም ከኢማን ባለቤት ጎን ነው። ይህንኑ በማስመልከት ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ሙእምን ሰው ነገሩ ሁሉ አስደናቂ ነው። የርሱ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው፤ይህ ለማንም ሳይሆን ለአማኝ ሰው ብቻ የሚሆን ነው። አስደሳች ነገር ሲያጋጥመው ያመሰግናል፣በጎም ይሆንለታል። ክፉ ነገር ቢያጋጥመውም ይታገሳል፣በጎም ይሆንለታል።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

ኢማን ባለቤቱን ችግር ሲያጋጥመው እንዲታገስ፣አሰደሳች ነገር ሲያጋጥመው ደግሞ አላህን እንዲያመሰግን ያደርገዋል።

13-

ኢማን አማኙን በከባዳ ኃጢአቶች ላይ እንዳይወድቅ መከላከያ ይሆነዋል። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹ዝሙተኛ ሰው ዝሙት በሚፈጽምበት ጊዜ፣አማኝ ሆኖ አይፈጽምም . . ››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

እነዚህ ውድና ክቡር የሆኑ የኢማን ፍሬዎች ናቸው። ታዲያ መታደልን፣ደስተኝነት፣የሕሊና ሰላምና የመንፈስ እርካታን የሚሹት ወዴት ነው ያሉት?!

የኢማን አሻራዎች፦

ኢማን በአንድ ሙእምን ሕይወት ውስጥ ከሚኖረው አሻራዎች መካከል የሚከተሉትን እናገኛለን፦

1-

አማኙ፣ለጠራው እስላማዊ ሸሪዓ ተመሪና ተገዥ ለመሆን ያለውን ጉጉት ይጨምራል። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّمَا كَانَ قَوۡلَ ٱلۡمُؤۡمِنِينَ إِذَا دُعُوٓاْ إِلَى ٱللَّهِ وَرَسُولِهِۦ لِيَحۡكُمَ بَيۡنَهُمۡ أَن يَقُولُواْ سَمِعۡنَا وَأَطَعۡنَاۚ وَأُوْلَٰٓئِكَ هُمُ ٱلۡمُفۡلِحُونَ ٥١)

‹‹የምእምናን ቃል የነበረው፣ወደ አላህና ወደ መልክተኛው፣በተጠሩ ጊዜ ሰማን፤ታዘዝንም፣ማለት ብቻ ነው፤እነዚህም እነሱ የፈለጉትን የሚያገኙ ናቸው።››

[አልኑር፡51]

ኢማን ባለቤቱን ለአላህ ትእዛዛት ተገዥና ተመሪ ለመሆን ተነሳሽነት እንዲኖረው ያደርጋል።

በአላህ ማመን ሕይወት ነው . . ከአላህ ጋር አብሮነትም ኢማን ነው።

አላህ ﷻ እንዲህ ይላል፦

(فَلَا وَرَبِّكَ لَا يُؤۡمِنُونَ حَتَّىٰ يُحَكِّمُوكَ فِيمَا شَجَرَ بَيۡنَهُمۡ ثُمَّ لَا يَجِدُواْ فِيٓ أَنفُسِهِمۡ حَرَجٗا مِّمَّا قَضَيۡتَ وَيُسَلِّمُواْ تَسۡلِيمٗا ٦٥)

‹‹በጌታህም እምላለሁ (አላህ በራሱ መማሉ ነው) በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ፣ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም (ምእምን አይሆኑም)።››

[አልኒሳእ፡65]

ይልቁንም ኢማን ባለቤቱን የአላህን ﷻትእዛዛት ወዶና ፈቅዶ በደስታ እንዲቀበል ያደርገዋል።

2-

አላህ አማኝ ባሪያውን ከግልጽና ከስውር ሽርክ (ማጋራት) እንዲጠበቅ ያደርገዋል። ይህም ጸሎቱን፣ረድኤትና እገዛ ፍለጋውን፣ምልጃና ተማጽኖውን ከአላህﷻ በስተቀር ለማንምና ለምንም ከማቅረብ በመራቅ ነው። እውነተኛው ጥቅም ሰጭና ጉዳት አስወጋጅም አላህ ብቻ ነውና። አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَإِن يَمۡسَسۡكَ ٱللَّهُ بِضُرّٖ فَلَا كَاشِفَ لَهُۥٓ إِلَّا هُوَ)

‹‹አላህም በጉዳት ቢነካህ ለርሱ (ለጉዳቱ) ከእርሱ በቀር ሌላ አስወጋጅ የለም፤››

[አልአንዓም፡17]

3-

ለአላህ ብሎ መውደድና ለአላህ ብሎ መጥላት የጠበቀ የኢማን ዘለበት ነው። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّمَا ٱلۡمُؤۡمِنُونَ إِخۡوَةٞ)

‹‹ምእመናኖች ወንድማማቾች ናቸው፤››

[አልሑጁራት፡10]

ለዚህ ትልቁ ማስረጃ፣በአንሷርና በሙሃጅሮች መካከል የተመሰረተው ወንድማማችነት ሲሆን፣አንሷር ለወንድሞቻቸው ሀብትና ንብረታቸውን በማጋራትና በመስጠት እስላማዊ ተራድኦን ተግባራዊ አድርገዋል። ታላቁ ነቢይﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹አንዳችሁ ለራሱ የወደደውን ነገር ለወንድሙ እስኪወድለት ድረስ (የተሟላ) አማኝ አይሆንም።››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

አላህ ﷻ ፦

(يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓاْ ءَامِنُواْ)

‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! . . . እመኑ፤››

በማለት የኢማንን ታላቅ ደረጃ በማመልከት ምእመናንን ወደ ኢማን እንዲመጡ በመገፋፋት ጥሪ አድርጎላቸዋል።

4-

በአላህ መንገድ በመታገል (በጅሃድ) ላይ መጽናት፣የአላህ ﷻ ውዴታ ለማግኘት ሲባል ውድና ክቡር የሆነውን ሁሉ በዚህ ላይ ማዋል። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّمَا ٱلۡمُؤۡمِنُونَ ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ بِٱللَّهِ وَرَسُولِهِۦ ثُمَّ لَمۡ يَرۡتَابُواْ وَجَٰهَدُواْ بِأَمۡوَٰلِهِمۡ وَأَنفُسِهِمۡ فِي سَبِيلِ ٱللَّهِۚ أُوْلَٰٓئِكَ هُمُ ٱلصَّٰدِقُونَ ١٥)

‹‹(እውነተኞቹ) ምእምናን እነዚያ በአላህና በመልክተኛው ያመኑት፣ከዚያም ያልተጠራጠሩት፣በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸውም በአላህ መንገድ የታገሉት ብቻ ናቸው፤እነዚያ እነሱ እውነተኞቹ ናቸው።››

[አልሑጁራት፡15]

5-

የአማኙ ልብ ከአላህ፣ከቀጠሮው፣ከቃል ኪዳኑ፣እርሱ ዘንድ ተስፋ ከሚያደርገውና ከዚህ ሁሉ ከሚያገኘው ደስተኝነት ጋር የተሳሰረ መሆኑ። ለርሱ የዱንያ ሕይወቱ ጀነት ኢማንና አላህን መታዘዝ ሲሆን፣አላህﷻ ቃል የገባለትን የኣኽራ ዘለዓዘለማዊ ሕይወት ጀነትን በተስፋ ይጠባበቃል። ከዚህም በላይ በዚህ ዓለም ሕይወቱ ለደረሰበት ድካም፣ችግርና ልፋት ሁሉ እርሱ ዘንድ ከመልካም ሥራዎቹ ጋር የሚመዘገብለትን ምንዳ ከአላህ ተስፋ ያደርጋል። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(مَا كَانَ لِأَهۡلِ ٱلۡمَدِينَةِ وَمَنۡ حَوۡلَهُم مِّنَ ٱلۡأَعۡرَابِ أَن يَتَخَلَّفُواْ عَن رَّسُولِ ٱللَّهِ وَلَا يَرۡغَبُواْ بِأَنفُسِهِمۡ عَن نَّفۡسِهِۦۚ ذَٰلِكَ بِأَنَّهُمۡ لَا يُصِيبُهُمۡ ظَمَأٞ وَلَا نَصَبٞ وَلَا مَخۡمَصَةٞ فِي سَبِيلِ ٱللَّهِ وَلَا يَطَُٔونَ مَوۡطِئٗا يَغِيظُ ٱلۡكُفَّارَ وَلَا يَنَالُونَ مِنۡ عَدُوّٖ نَّيۡلًا إِلَّا كُتِبَ لَهُم بِهِۦ عَمَلٞ صَٰلِحٌۚ إِنَّ ٱللَّهَ لَا يُضِيعُ أَجۡرَ ٱلۡمُحۡسِنِينَ ١٢٠ وَلَا يُنفِقُونَ نَفَقَةٗ صَغِيرَةٗ وَلَا كَبِيرَةٗ وَلَا يَقۡطَعُونَ وَادِيًا إِلَّا كُتِبَ لَهُمۡ لِيَجۡزِيَهُمُ ٱللَّهُ أَحۡسَنَ مَا كَانُواْ يَعۡمَلُونَ ١٢١)

‹‹ለመዲና ሰዎችና ከአዕራብም በዙሪያቸው ላሉት ሰዎች፣ከአላህ መልክተኛ ወደኋላ ሊቀሩ፣ነፍሶቻቸውንም ከነፍሱ አብልጠው ሊወዱ አይገባቸውም ነበር፤ይህ (ከመቅረት መከልከል) ለነርሱ መልካም ሥራ የሚጻፍላቸው ቢኾን እንጅ፣በአላህ መንገድ ላይ ጥምም ድካምም፣ረኃብም፣የማይነካቸው፣ከሐዲዎችንም የሚያስቆጭን ስፍራ የማይረግጡ፣ከጠላትም የሚጎዳን ነገር (መግደልን መማረክን መዝረፍን) የማያገኙ፣በመኾናቸው ነው። አላህ የመልካም ሥራዎችን አያጠፋምና። ትንሽንም ትልቅንም ልግስና አይለግሱም፣ወንዝንም አያቋርጡም፣አላህ ይሠሩት ከነበረው የበለጠን ምንዳ ይመነዳቸው ዘንድ ለነሱ የሚጽፍላቸው ቢኾን እንጅ።››

[አልተውባህ፡120-121]

ይህ ሁሉ ከአላህﷻ ጋር ባላቸው ግንኙነት ሐቀኞችና ፍጹም ለሆኑ የኢማን ባለቤቶች የተዘጋጀ ነው።

6-

የአላህንና የመልክተኛውን ረዳትነትና ወዳጅነታቸውን ማግኘት። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(إِنَّمَا وَلِيُّكُمُ ٱللَّهُ وَرَسُولُهُۥ وَٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ)

‹‹ረዳታችሁ አላህና መልክተኛው፣እነዚያም ያመኑት ብቻ ናቸው፤››

[አልማእዳህ፡55]

የአላህን ረዳትነት (ውላያ) ማግኘት ማለት እርሱን መውደድ፣ለሃይማኖቱ እገዛና ድጋፍ ማድረግ፣ወዳጆቹን መወዳጀት፣ጠላቶቹን ማግለልና ራስን ከዚያ ነጻ ማድረግ ማለት ነው። አላህ ﷻ እንዲህ ብሏል፦

(لَّا تَجِدُ قَوۡمٗا يُؤۡمِنُونَ بِٱللَّهِ وَٱلۡيَوۡمِ ٱلۡأٓخِرِ يُوَآدُّونَ مَنۡ حَآدَّ ٱللَّهَ وَرَسُولَهُۥ وَلَوۡ كَانُوٓاْ ءَابَآءَهُمۡ أَوۡ أَبۡنَآءَهُمۡ أَوۡ إِخۡوَٰنَهُمۡ أَوۡ عَشِيرَتَهُمۡۚ أُوْلَٰٓئِكَ كَتَبَ فِي قُلُوبِهِمُ ٱلۡإِيمَٰنَ وَأَيَّدَهُم بِرُوحٖ مِّنۡهُۖ وَيُدۡخِلُهُمۡ جَنَّٰتٖ تَجۡرِي مِن تَحۡتِهَا ٱلۡأَنۡهَٰرُ خَٰلِدِينَ فِيهَاۚ رَضِيَ ٱللَّهُ عَنۡهُمۡ وَرَضُواْ عَنۡهُۚ أُوْلَٰٓئِكَ حِزۡبُ ٱللَّهِۚ أَلَآ إِنَّ حِزۡبَ ٱللَّهِ هُمُ ٱلۡمُفۡلِحُونَ ٢٢)

‹‹በአላህና በመረሻው ቀን የሚያምኑትን ሕዝቦች አላህንና መልክተኛውን የሚከራከሩትን ሰዎች፤አባቶቻቸው ወይም ልጆቻቸው፤ወይም ወንድሞቻቸው ወይም ዘመዶቻቸው ቢኾንም እንኳ የሚወዳጁ ኾነው አታገኛቸውም፤እነዚያ በልቦቻቸው ውስጥ እምነትን ጽፏል፤ከርሱም በኾነ መንፈስ ደግፏቸዋል፤ከሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ ያገባቸዋል፤አላህ ከነርሱ ወዷል። ከርሱም ወደዋል፤እነዚያ የአላህ ሕዝቦች ናቸው፤ንቁ፣የአላህ ሕዝቦች እነሱ ምኞታቸውን የሚያገኙ ናቸው።››

[አልሙጃደላህ፡22]

ይልቅዬ አማኝ ሰው አላህንና ረሱልን፣ምእመናንንም የሚወዳጃቸው ሲሆን፣ ከሓዲዎችን ፈጽሞ ወዳጆቹ አድርጎ አይይዝም። ይህን አስመልክቶ አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(لَّا يَتَّخِذِ ٱلۡمُؤۡمِنُونَ ٱلۡكَٰفِرِينَ أَوۡلِيَآءَ مِن دُونِ ٱلۡمُؤۡمِنِينَ)

‹‹ምእምናን፣ከሓዲዎችን ከምእምናን ሌላ ረዳቶች አድርገው አይያዙ፤››

[ኣል ዒምራን፡28]

7-

መልካም ስነምግባርና የተገራ ጠባይ የሚያስገኝ መሆኑ። ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹(አላህን) ማፈር (ሐያእ) እና ኢማን አንድ ላይ የተቆራኙ ናቸው፤አንደኛው ሲጠፋ ሌላኛውም ይጠፋል››

(በበይሀቂ የተዘገበ)

የዓይነ አፋርነትና የይሉኝታ ጠባይ ከታላላቅ ስነምግባሮች አንዱ ሲሆን፣አማኝ ሰው ችግር፣መከፋፈል፣መቀያየም . . . የሌለበትን የተድላ ሕይወት ከወንድሞቹ ጋር በአብሮነት መኖር ይችል ዘንድ ጠባዩንና ስነምግባሩን ያሳምራል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ሙእምን በመሆኑ ሲሆን አማኝ ያልሆነ ሰው ግን አይታደለውም።

8-

ሙእምን ሰው፣አንድ ጌታ አላህን ﷻ ፣አንድ ነቢይ ታላቁ ሙሐመድን ﷺ ፣አንድ መመሪያ የአላህን ውዴታ መከተልን፣አንድ ዓለማ ምድርና ሰማያትን ያህል የሚሰፋውን ጀነትን ያለው በመሆኑ፣እውነተኛው ደስታና የመንፈስ እርካታ፣በዱንያ ላይ ሆኖ ጀነት ውስጥ እንዳለ ሆኖ እንዲሰማው ያደርገዋል።

የስነልቦና ሕክምና ክሊኒኮች በየቦታው በህሙማን ተሞልተው ይታያሉ። ስለ ጭንቀት፣ስለ ውጥረት፣ስለ እንቅልፍ ማጣት፣ስለ ፍርሃትና አስፈሪ ቅዠት . . የሚነገረውን ስንሰማ፣ይህ ሁሉ በአላህ ﷻ እውነተኛ የሆነ እምነት ከማመን በመራቅ፣በዓለማዊ ሕይወት ላይ ብቻ በመንጠላጠልና በቁሳዊነት በመዘፈቅ ምክንያት የመጣ መሆኑን በእርግጠኝነት እንረዳለን። ቁሳዊው የሕይወት ጎን በመንፈሳዊው ጎን ላይ አይሎ ድንበር የጣሰ በመሆኑ፣ለሰው ልጅ መንፈሳዊ ጎኑን ማርካት እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ይታያል። ይህ እውን ሊሆን የሚችለው ግን በአላህ ﷻ እውነተኛ የሆነ እምነት በማመን፣በርሱ በመንጠላጠል፣ሁሌ እርሱን በማስታወስና በማወደስ፣በመላእኮቹ፣በመጽሐፎቹ፣በመልክተኞቹ፣በመጨረሻው ቀንና፣በጎውም ሆነ ክፉው፣ጣፋጩም ሆነ መራራው በአላህ ውሳኔ መሆኑን በማመን ብቻ ነው።

በጣም አሳሳቢው ነገር፣ጣፊዋን የዱንያ ምድራዊ ሕይወት መጠቀሚዎችን በስግብግብነት ሲያሳድዱ ብዙ ሰዎች የልቦና ፈውስንና የሕሊና ሰላምን የዘነጉ መሆናቸው ነው። በዚህም የሚስገበገቡለትን ቁሳዊ ጥቅምም እውን ሳያደርጉ ወይም የህሊና ሰላምና የመንፈስ እርካታንም ሳያገኙ ከንቱ ይቀራሉ።

የሕይወትን መንፈሳዊ ጎን ማርካት የሚቻለው በኢማን ብቻ ነው። መንፈስ ወይም ሩሕ ከርሱ ዘንድ ሲሆን፣ገላ ግን አላህ ከአፈር የፈጠረው በመሆኑ፣የሰው መንፈሳዊ ጎን በረካ ቁጥር ነፍስ ትመጥቃለች፤ትረጋጋለች፤ከትናንሽ ጉዳዮችም ከፍ ትላለች። ይህ ጎን ችላ በተባለና በተዘነጋ ቁጥር ደግሞ፣ነፍስያ ወደ እንስሳዊ ሥጋዊ ባሕርይ ታዘቀዝቃለች፤ውጥረቷና ስቃይ መከራዋም እየጨመረ ይሄዳል፤ዓለም ይጨልምባታል።



Tags: