3- አላህንﷻ መፍራት (አልኸውፍ) ፦

3- አላህንﷻ  መፍራት (አልኸውፍ) ፦
(وَيُحَذِّرُكُمُ ٱللَّهُ نَفۡسَهُ) [آل عمران: 30]

‹‹አላህ ነፍሱን ያስጠነቅቃችኋል።›› [ኣል ዒምራን፡30]

የፍርሃት (ኸውፍ) ጽንሰ ሀሳብ ፦

አላህን መፍራት ከታላላቅ የልቦና ዕባዳዎች አንዱ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِنَّمَا ذَٰلِكُمُ ٱلشَّيۡطَٰنُ يُخَوِّفُ أَوۡلِيَآءَهُۥ فَلَا تَخَافُوهُمۡ وَخَافُونِ إِن كُنتُم مُّؤۡمِنِينَ ١٧٥)

‹‹ይሃችሁ፣ሰይጣን ብቻ ነው፣ወዳጆቹን ያስፈራራችኋል፤አትፍሩዋቸውም፤ምእምናንም እንደኾናችሁ ፍሩኝ።››

[ኣል ዒምራን፡175]

ከዚህ አንቀጽ አንድ አላህን ብቻ መፍራት ግዴታ መሆኑን፣ለኢማን መሟላት ካለባቸው ነገሮችም አንዱ መሆኑ በአጽንኦት ተገልጿል። አንድ ሰው አላህን የሚፈራው በኢማኑ ጥንካሬ መጠን ነው።

እመ ምእመናን ዓእሻ (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋል ፦

ነቢዩንﷺ ስለዚህ አንቀጽ ጠየቅኋቸው ፦

(وَٱلَّذِينَ يُؤۡتُونَ مَآ ءَاتَواْ وَّقُلُوبُهُمۡ وَجِلَةٌ)؛

‹‹እነዚያም የሚሰጡትን ነገር እነርሱ ወደ ጌታቸው ተመላሾች መኾናቸውን፣ልቦቻቸው የሚፈሩ ኾነው የሚሰጡት።››

እነዚህ አስካሪ መጠጥ የሚጠጡና የሚሰርቁ ናቸውን?! ‹‹የአስሲድዲቅ ልጅ ሆይ! አይደሉም፤ግና እነዚያ ተቀባይነት እንዳያጡ እየፈሩና እየሰጉ የሚጾሙ፣የሚሰግዱና ምጽዋት የሚሰጡ ናቸው›› አሉ።

(በትርምዚ የተዘገበ)

አላህንﷻ ለመፍራት የሚገፋፉ ነገሮች ፦

1-

ስሞቹንና ባሕርያቱን አስመልክቶ በሚኖር ዕውቀት ምክንያት፣ለኃያልነቱና ለግርማ ሞገሱ ተገቢ በሆነ ሁኔታ አላህንﷻ ማክበርና ማላቅ።

(يَخَافُونَ رَبَّهُم مِّن فَوۡقِهِمۡ)

‹‹‹ጌታቸውን ከበላያቸው ሲኾን ይፈሩታል፤››

[አልነሕል፡50]

2-

የፍጻሜው መጨረሻ ወደሚጠላውና ወደ አስከፊው አሳማሚ የገነም እሳት እንዳይሆን መፍራት ።

3-

ሙእምን ሰው አላህﷻ ነገሩን ሁሉ የሚያይና በዝርዝር የሚያውቀው መሆኑን፣በርሱ ላይም ፍጹማዊ ሥልጣን ያለው መሆኑን መገንዘብ፣ያሉበትን ግዴታዎች በመወጣት ረገድ ተገቢውን ያደረጉ የመሆንን ስሜት ሁሌም ማሳደር። ጥፋት ከፈጸመበት ኃያል ፈጣሪ ታላቅነት አንጻር የተፈጸመውን ጥፋትም አቅልሎ አለመመልከት።

4-

በርሱ ላይ ባመጸና ከሸሪዓው ባፈነገጠ፣ወደርሱ የተላከውን ብርሃን ችላ ባለ ሰው ላይ በተላለፈ ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ የተሞላውን የአላህንﷻ ንግግር አስተውሎ ማስተንተን።

5-

ቁርኣንና የነቢዩን ሐዲሥ አስተውሎ መረዳትና የነቢዩንﷺ የሕይወት ታሪክ (ሲራ) ማጥናት።

6-

የ አላህንﷻ ኃያልነት ማሰብ ማሰላሰልና ማስተንተን። ይህን አስተንትኖ ያስተዋለ ሰው፣የላቁ ባሕርያቱን (ስፋቱን)፣ግርማ ሞገሱንና ኃያልነቱን ይረዳል። ልቡ የአላህንﷻ ኃያልነትና ግርማ ሞገሱን የመሰከረ ሰውም፣የርሱ ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ምን ማለት እንደሆነ የግድ ይገነዘባል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَيُحَذِّرُكُمُ ٱللَّهُ نَفۡسَهُۥ)

‹‹አላህ ነፍሱን ያስጠነቅቃችኋል።››

[ኣል ዒምራን፡28]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَمَا قَدَرُواْ ٱللَّهَ حَقَّ قَدۡرِهِۦ وَٱلۡأَرۡضُ جَمِيعٗا قَبۡضَتُهُۥ يَوۡمَ ٱلۡقِيَٰمَةِ وَٱلسَّمَٰوَٰتُ مَطۡوِيَّٰتُۢ بِيَمِينِهِ)

‹‹አላህንም በትንሣኤ ቀን ምድር በመላ (አንድ) ጭብጡ ስትኾን፤ሰማያትም በኃይሉ የሚጠቀለሉ ሲኾኑ፣(ከርሱ ጋር ሌላን በማጋራታቸው) ተገቢ ክብሩን አላከበሩትም።››

[አልዙመር፡67]

አላህን መፍራት እርሱን ማወቅ ያስከትላል። እርሱን ማወቅ ደግሞ እረሱን መስጋት ያስከትላል። ቅጣቱንና ማስጠንቀቂያውን መስጋት ደግሞ ለርሱ ተገዥና ታዛዥ መሆንን ያስገኛል።

7-

ሞትና ጭንቁን፣ደራሽና አይቀሬ መሆኑን ማሰብና ማስተንተን ፦

(قُلۡ إِنَّ ٱلۡمَوۡتَ ٱلَّذِي تَفِرُّونَ مِنۡهُ فَإِنَّهُۥ مُلَٰقِيكُمۡ)

‹‹ያ ከርሱ የምትሸሹት ሞት እርሱ በእርግጥ አግኛችሁ ነው፤››

[አልጁሙዓህ፡8]

ሞት ለአላህ ያለንን ፍራቻ ይጨምራል። ነቢዩﷺ ከእንዲህ ብለዋል፦

‹‹የደስታና የእርካታዎችን ቆራጭ (ሞትን) ማስታወስ አብዙ፤በጭንቅ ኑሮ ላይ ሆኖ ያስታወሰው ማንኛውም ሰው (ኑሮው) ይሰፋለታል፤በድሎት ላይ ሆኖ ያስታወሰው ማንኛውም ሰው ደግሞ (ምንም ቢደላው ድሎቱን) ይጠብበታል።››

(በጠበራኒ የተዘገበ)

8-

ከሞት በኋላ ያሉትን ነገሮች፣መቃብርንና በውስጡ ያሉ አስበርጋጊ ሁኔታዎችን ማሰብና ማስተንተን። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል፦

‹‹መቃብሮችን ከመጎብኘት ከልክያችሁ ነበር፣ኣኽራን (የወዲያኛውን ዓለም) ስለሚያስታውሷችሁ ጎብኟቸው፡››

(በእብን ማጃህ የተዘገበ)

በራእ  የሞከተለውን አስተላልፈዋል፦

‹‹በአንድ የቀብር ስነ ሥርዓት ላይ ከአላህ መልክተኛﷺ ጋር ነበርን፤በመቃብሩ አፋፍ ላይ ተቀመጡና አፈሩ እስኪረጥብ ድረስ አለቀሱ፤ከዚያም፦ ወንድሞቼ ሆይ! ለእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ራሳችሁን አዘጋጁ፣አሉን።››

(በእብን ማጃህ የተዘገበ)

አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(يَٰٓأَيُّهَا ٱلنَّاسُ ٱتَّقُواْ رَبَّكُمۡ وَٱخۡشَوۡاْ يَوۡمٗا لَّا يَجۡزِي وَالِدٌ عَن وَلَدِهِۦ وَلَا مَوۡلُودٌ هُوَ جَازٍ عَن وَالِدِهِۦ شَيًۡٔاۚ إِنَّ وَعۡدَ ٱللَّهِ حَقّٞۖ فَلَا تَغُرَّنَّكُمُ ٱلۡحَيَوٰةُ ٱلدُّنۡيَا وَلَا يَغُرَّنَّكُم بِٱللَّهِ ٱلۡغَرُورُ ٣٣)

‹‹እላንተ ሰዎች ሆይ! ጌታችሁን ፍሩ፤ወላጅም ከልጁ (በምንም) የማይጠቅምበትን፣ተወላጅም እርሱ ወላጅን በምንም ጠቃሚ የማይኾንበትን ቀን ፍሩ፤የአላህ ቀጠሮ እውነት ነውና፤ቅርቢቱም ሕይወት አትሸንግላችሁ፤በአላህም (መታገስ) አታላዩ (ሰይጣን) አያታላችሁ።››

[ሉቅማን፡33]

9-

ሰዎች አሳንሰው የሚመለከቷቸው ጥቃቅን ኃጢአቶች ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብና ማስተነትን። ነቢዩﷺ ጉዳዩን በምሳሌ አስቀምጠውልናል። የሰዎች ስብስብ አንድ ሸለቆ ላይ ሰፈረሩና እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ እንጨት አምጥቶ ምግባቸውን ማብሰል የሚያስችል ማገዶ መሰብሰብ ቻሉ። ጥቃቅን እንጨቶች ተሰብስበው ምግቡን እንዳበሰሉ ሁሉ፣ጥቃቅን ኃጢአቶችም ተሰብስበው የኃጢአንን ገላ በገሀነም እሳት ያቃጥላሉ ፦

(كُلَّمَا نَضِجَتۡ جُلُودُهُم)

‹‹ቆዳዎቻቸው በተቃጠሉ ቁጥር ሌሎችን ቆዳዎች እንለውጥላቸዋለን፤››

[አልኒሳእ፡56]

10-

አንድ የአላህ ባሪያ በኃጢአቱ ተጸጽቶ ተውበት ከማድረጉ በፊት በድንገተኛ ሞት ሊቀደም እንዲችል ማወቅ ይኖርበታል። ጊዜው ካለፈ በኋላ መጸጸት ጥቅም የለውም። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(حَتَّىٰٓ إِذَا جَآءَ أَحَدَهُمُ ٱلۡمَوۡتُ قَالَ رَبِّ ٱرۡجِعُونِ ٩٩)

‹‹አንዳቸውንም ሞት በመጣባቸው ጊዜ፣እንዲህ ይላል፦ ጌታዬ ሆይ! (ወደ ምድረ ዓለም) መልሱኝ፤››

[አልሙእሚኑን፡99]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَأَنذِرۡهُمۡ يَوۡمَ ٱلۡحَسۡرَةِ)

‹‹የቁጭቱን ቀን አስፈራራቸው።››

[መርየም፡39]

11-

ክፉ ፍጻሜን (ሱኡል ኃትማ) ማሰብና ማስተንተን። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(ٱلۡمَلَٰٓئِكَةُ يَضۡرِبُونَ وُجُوهَهُمۡ وَأَدۡبَٰرَهُمۡ)

‹‹መላእክት ፊቶቻቸውንና ጀርቦቻቸውን እየመቱ . . ››

[አልአንፋል፡50]

12-

ፈሪሃ አላህ እንዲያድርብህና እርሱን እንድትፈራ ከሚያደርጉህ ሰዎች ጋር መቀመጥ። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَٱصۡبِرۡ نَفۡسَكَ مَعَ ٱلَّذِينَ يَدۡعُونَ رَبَّهُم بِٱلۡغَدَوٰةِ وَٱلۡعَشِيِّ يُرِيدُونَ وَجۡهَهُۥ)

‹‹ነፍስህንም፣ከነዚያ ጌታቸውን ፊቱን (ውዴታውን) የሚሹ ኾነው በጧትና በማታ ከሚግገዙት ጋር አስታግስ፤››

[አልከህፍ፡28]

አላህን መፍራት ከሁለት ነገሮች ጋር የተያያዘ ነው ፦

ሀ- ቅጣቱን ከመፍራት ፦

ይህ ከርሱ ጋር ሌላን ለአጋራው፣ኃጢአት ለፈጸመውና በትእዛዛቱ ላይ ላመጸው የተሰናዳውን አስከፊ ቅጣቱን መፍራት ነው።

ለ- አላህን ከመፍራት ፦

ይህ ደግሞ ዓሊሞችና እርሱን ያወቁ ጻድቃን ባሮቹ የሚፈሩት የፍርሃት ዓይነት ነው ፦

(وَيُحَذِّرُكُمُ ٱللَّهُ نَفۡسَهُ)

‹‹አላህ ነፍሱን ያስጠነቅቃችኋል።››

[ኣል ዒምራን፡28]

ስለ አላህﷻ የሚኖረው ዕውቀት በጨመረ ቁጥር እርሱን መፍራትም እየጨመረ ይሄዳል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِنَّمَا يَخۡشَى ٱللَّهَ مِنۡ عِبَادِهِ ٱلۡعُلَمَٰٓؤُاْ)

‹‹አላህን ከባሮቹ ውስጥ የሚፈሩት፣ዐዋቂዎቹ ብቻ ናቸው፤››

[ፋጢር፡28]

ለጌታቸው ለአላህﷻ ፣ለስሞቹና ለባሕርያቱ ያላቸው ዕውቀት የተሟላ በሚሆንበት ጊዜ፣ከምንም በላይ እርሱን መፍራት ስለሚመርጡ ተጽእኖውና አሻራው በአካላዊ ድርጊቶች ላይ አርፎ ይስተዋላል።

የአላህ ፍርሃት ልብ ውስጥ ከሰፈረ፣የስሜታዊ ዝንባሌዎችንና የቁሳዊ ፍላጎቶችን ሰፈሮች አቃጥሎ ዱንያን ከልብ ያስወጣል።

አላህን መፍራት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ ፦

ሀ- በቅርቢቱ የዱንያ ሕይወት ፦

1-

በምድር ላይ መመቻቸትን ከሚያመጡ፣ ኢማንን ከሚያፋፉና መረጋጋትን ከሚያስገኙ ምክንያቶች አንዱ ነው። ቃል የተገባ ነገር ተፈጽሞ ሲገኝ መተማመንን ይጨምራል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(وَقَالَ ٱلَّذِينَ كَفَرُواْ لِرُسُلِهِمۡ لَنُخۡرِجَنَّكُم مِّنۡ أَرۡضِنَآ أَوۡ لَتَعُودُنَّ فِي مِلَّتِنَاۖ فَأَوۡحَىٰٓ إِلَيۡهِمۡ رَبُّهُمۡ لَنُهۡلِكَنَّ ٱلظَّٰلِمِينَ ١٣ وَلَنُسۡكِنَنَّكُمُ ٱلۡأَرۡضَ مِنۢ بَعۡدِهِمۡۚ ذَٰلِكَ لِمَنۡ خَافَ مَقَامِي وَخَافَ وَعِيدِ ١٤)

‹‹እነዚያም የካዱት፣ለመልክተኞቻቸው ፦ ከምድራችን በእርግጥ እናወጣችኋለን፤ወይም ወደ ሃይማኖታችን በእርግጥ ትመለሳላችሁ፣አሉ፤ወደነርሱም ጌታቸው እንዲህ ሲል ላከ ፦ ከሓዲዎችን በእርግጥ እናጠፋለን። ከነሱም በኋላ ምድሪቱን በእርግጥ እናስቀምጣችኋለን፤ይኸ በፊቴ መቆሙን ለሚፈራ፣ዛቻየንም ለሚፈራ ሰው ነው።››

[ኢብራሂም፡13-14]

2-

በበጎ ሥራዎችና በልቦና ፍጹምነት (እኽላስ) ላይ ያበረታታል። የኣኽራው ታላቅ ምንዳ ሳይቀንስ በዱንያ ላይ መካካሻ ያለመፈለግ ተነሳሽነትን ያነቃቃል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِنَّمَا نُطۡعِمُكُمۡ لِوَجۡهِ ٱللَّهِ لَا نُرِيدُ مِنكُمۡ جَزَآءٗ وَلَا شُكُورًا ٩ إِنَّا نَخَافُ مِن رَّبِّنَا يَوۡمًا عَبُوسٗا قَمۡطَرِيرٗا ١٠)

‹‹የምናበላችሁ ለአላህ ውዴታ ብቻ ነው፤ከናንተ ዋጋንም ማመስገንንም አንፈልግም። እኛ (ፊትን) የሚያጨፈግግን ብርቱ ቀን ከጌታችን እንፈራለንና፤(ይላሉ)።››

[አልደህር፡9-10]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(فِي بُيُوتٍ أَذِنَ ٱللَّهُ أَن تُرۡفَعَ وَيُذۡكَرَ فِيهَا ٱسۡمُهُۥ يُسَبِّحُ لَهُۥ فِيهَا بِٱلۡغُدُوِّ وَٱلۡأٓصَالِ ٣٦ رِجَالٞ لَّا تُلۡهِيهِمۡ تِجَٰرَةٞ وَلَا بَيۡعٌ عَن ذِكۡرِ ٱللَّهِ وَإِقَامِ ٱلصَّلَوٰةِ وَإِيتَآءِ ٱلزَّكَوٰةِ يَخَافُونَ يَوۡمٗا تَتَقَلَّبُ فِيهِ ٱلۡقُلُوبُ وَٱلۡأَبۡصَٰرُ ٣٧)

‹‹አላህ እንድትከበርና ስሙ በውስጧ እንዲወሳ ባዘዘው ቤቶች ውስጥ፣(አወድሱት)፤በውስጧ፣በጧትና በማታ ለርሱ ያጠራሉ፣አላህን ከማውሳትና ሶላትን ከመስገድ፣ዘካንም ከመስጠት፣ንግድም ሽያጭም የማያታልላቸው፣ልቦችና ዓይኖች በርሱ የሚገለባበጡበትን ቀን የሚፈሩ የኾኑ ሰዎች፣(ያጠሩታል)።››

[አልኑር፡36]

ልቦችና ዓይኖች በርሱ የሚገለባበጡበትን ቀን የሚፈሩ መሆናቸው፣መድህን እንዲፈልጉ፣አስፈሪውን ቀን እንዲጠነቀቁና መዝገባቸውን በግራ እንዳይቀበሉ በመስጋት ለበጎ ሥራ እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል።

የአላህ ፍርሃት ልብ ውስጥ ከሰፈረ የስሜታዊ ዝንባሌዎችንና የቁሳዊ ፍላጎቶችን ሰፈሮች አቃጥሎ ዱንያን ከልብ ያስወጣል።

አላህን የፈራ ሰው ፍርሃቱ ወደ በጎ ነገር ሁሉ ይመራዋል።

ለ- በወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት ፦

1-

ባሪያው በትንሣኤ ቀን በአላህንﷻ ዙፋን (ዐርሽ) ጥላ ስር ይሆናል። የአላህ መልክተኛﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ማዕረግና ቁንጅና ያላት ሴት (ለዝሙት) ጠይቃው፣እኔ አላህን እፈራለሁ ያለ ሰው፣ . . . ››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

ከሐዲሡ በግልጽ የምንረዳው ሴቲቱን ከተግባሯ ለመገሰጽና ራሱንም ለመምከር በአንደበቱ የተናገረ መሆኑን ነው። መርሁን ካወጀ በኋላ በአቋሙ ጸንቶ ገፍቶ የቀጠለ መሆኑንም እንገነዘባለን።

‹‹(ሌላው) ለብቻው ሆኖ አላህን አስታውሶ ዓይኖቹ ያነቡ ሰው ነው . . .››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

ዓይኖችን እንዲያለቅሱ ያደረገ የአላህ ፍራቻ በትንሣኤ ቀን ዓይኑ በጀሀነም እሳት እንዳትነካ ያደርጋል ማለት ነው።

2-

ከአላህﷻ ምሕረት ለማግኘት ምክንያት ነው። ለዚህ ማስረጃው ቀጣዩ የነቢዩﷺ ሐዲሥ ነው ፦

‹‹ከናንተ በፊት በነበሩት ሕዝቦች ውስጥ አላህ ሀብት የሰጠው አንድ ሰው ነበር። ለሞት ሲያጣጥር ለወንዶች ልጆቹ እንዲህ አለ ፦ እንዴት ያለ አባት ነበርኩ? ምርጥ አባት ነበርክ፣አሉት። እኔ ፈጽሞ መልካም ነገር ሠርቼ አላውቅምና ሲሞት ሬሳዬን አቃጥሉ፤ከዚያም አድቅቃችሁ ፍጩኝ፤ከዚያም በነፋሻ ቀን አመዴን አየር ላይ በትኑት፣አላቸው። ያላቸውን ፈጸሙ። አላህﷻ ሰበሰበውና ፦ ይህን እንድታደርግ ያደረገህ ምንድን ነው? አለው። የአንተ ፍራቻ ነው አለ፤(አላህም) በርኅራሄው ተቀበለው።››

(በቡኻሪ የተዘገበ)

አላህﷻ አለአዋቂነቱን አይቶ ምክንያቱን ተቀብሎት፣ጌታውን መፍራቱም አማላጅ ሆነው እንጂ ዳግም ከሞት መቀስቀስን የሚክድ ሰው ካፍር ነው።

3-

አላህን መፍራት ባለቤቱን ወደ ጀነት ያደርሳል። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹የፈራ ሰው በሌሊቱ መመጀመሪያ ላይ ጉዞ ይጀምራል፤በሌሊቱ መመጀመሪያ ላይ የተጓዘም ካሰበበት ይደርሳል፤ንቁ! የአላህ ወረት (ዕቃ) ውድ ነው፤ንቁ! የአላህ ወረት (ዕቃ) ጀነት ነው።››

(በትርምዚ የተዘገበ)

4-

በትንሣኤ ቀን ጸጥታና መረጋጋትን ማግኘት። አላህﷻ ሐዲሥ አልቁድሲ ውስጥ እንዲህ ብሏል ፦

‹‹በኃያልነቴ ይሁንብኝ በባሪዬ ላይ ሁለት ፍርሃቶችንና ሁለት ጸጥታዎችን አላጣምርበትም፤በዱንያ ላይ ከፈራኝ በትንሣኤ ቀን ጸጥታና ደህንነት እሰጠዋለሁ፤በዱንያ ላይ የኔን አዘናግቶ መያዝ ያልፈራ ከሆነ ግን በትንሣኤ ቀን አስፈራዋለሁ።››

(በበይሀቂ የተዘገበ)

5-

አላህንﷻ በክብር ከገለጻቸው ትጉሃን ምእመናን አገልጋዮቹ ተርታ መቀላቀል። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(إِنَّ ٱلۡمُسۡلِمِينَ وَٱلۡمُسۡلِمَٰتِ وَٱلۡمُؤۡمِنِينَ وَٱلۡمُؤۡمِنَٰتِ وَٱلۡقَٰنِتِينَ وَٱلۡقَٰنِتَٰتِ وَٱلصَّٰدِقِينَ وَٱلصَّٰدِقَٰتِ وَٱلصَّٰبِرِينَ وَٱلصَّٰبِرَٰتِ وَٱلۡخَٰشِعِينَ وَٱلۡخَٰشِعَٰتِ وَٱلۡمُتَصَدِّقِينَ وَٱلۡمُتَصَدِّقَٰتِ وَٱلصَّٰٓئِمِينَ وَٱلصَّٰٓئِمَٰتِ وَٱلۡحَٰفِظِينَ فُرُوجَهُمۡ وَٱلۡحَٰفِظَٰتِ)

‹‹ሙስሊሞች ወንዶችና ሙስሊሞች ሴቶች፣ምእምናንና ምእምናትም፣ታዛዦች ወንዶችና ታዛዦች ሴቶችም፣እውነተኞች ወንዶችና እውነተኞች ሴቶችም፣ታጋሾች ወንዶችና ታጋሾች ሴቶችም፣አላህን ፈሪዎች ወንዶችና አላህን ፈሪዎች ሴቶችም፣መጽዋቾች ወንዶችና መጽዋቾች ሴቶችም፣ጿሚዎች ወንዶችና ጿሚዎች ሴቶችም፣(ካልተፈቀደ ሥራ) ብልቶቻቸውን ጠባቂዎች ወንዶችና ብልቶቻቸውን ጠባቂ ሴቶችም፣››

[አልአሕዛብ፡35]

እነዚህ ባሕርያት በነሱ ለመገለጽ ሁሉም ሰው መትጋት ያለበት ክቡር ባሕርያት ናቸው።

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(تَتَجَافَىٰ جُنُوبُهُمۡ عَنِ ٱلۡمَضَاجِعِ يَدۡعُونَ رَبَّهُمۡ خَوۡفٗا وَطَمَعٗا وَمِمَّا رَزَقۡنَٰهُمۡ يُنفِقُونَ ١٦ فَلَا تَعۡلَمُ نَفۡسٞ مَّآ أُخۡفِيَ لَهُم مِّن قُرَّةِ أَعۡيُنٖ جَزَآءَۢ بِمَا كَانُواْ يَعۡمَلُونَ ١٧)

‹‹ጌታቸውን ለመፍራትና ለመከጀል የሚጠሩት ኾነው፣ጎኖቻቸው ከመጋደሚያ ስፍራዎች ይራራቃሉ፤ከሰጠናቸውም (ጸጋ) ይለገሳሉ። ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት፣ከዓይኖች መርጊያ ለነሱ የተደበቀላቸውን (ጸጋ)፣ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም።››

[አልሰጅዳህ፡16]

በተጨማሪም አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(أَمَّنۡ هُوَ قَٰنِتٌ ءَانَآءَ ٱلَّيۡلِ سَاجِدٗا وَقَآئِمٗا يَحۡذَرُ ٱلۡأٓخِرَةَ وَيَرۡجُواْ رَحۡمَةَ رَبِّهِۦۗ قُلۡ هَلۡ يَسۡتَوِي ٱلَّذِينَ يَعۡلَمُونَ وَٱلَّذِينَ لَا يَعۡلَمُونَۗ إِنَّمَا يَتَذَكَّرُ أُوْلُواْ ٱلۡأَلۡبَٰبِ ٩)

‹‹እርሱ የመጨረሻይቱን ዓለም (ቅጣት) የሚፈራ፣የጌታውንም ችሮታ የሚከጅል ሲኾን፣በሌሊት ሰዓቶች ሰጋጅና ቋሚ ኾኖ ለጌታው የሚግገዛ ሰው፣(እንደ ተስፋ ቢሱ ከሓዲ ነውን? በለው)፤እነዚያ የሚያውቁና እነዚያ የማያውቁ ይተካከላሉን? በላቸው፤የሚገነዘቡት ባለ አእምሮዎቹ ብቻ ናቸው።››

[አልዙመር፡9]

አላህﷻ እንዲህ ብሏል፦

(وَٱلَّذِينَ هُم مِّنۡ عَذَابِ رَبِّهِم مُّشۡفِقُونَ ٢٧ إِنَّ عَذَابَ رَبِّهِمۡ غَيۡرُ مَأۡمُونٖ ٢٨)

‹‹እነዚያ እነሱ ከጌታቸው ቅጣት ፈሪዎች የኾኑት። የጌታቸው ቅጣት (መምጣቱ) የማያስተማምን ነውና።››

[አልመዓሪጅ፡27-28]

አላህንﷻ ከአገልጋዮቹ ሁሉ ይበልጥ ቅርቡ የሆኑትን ነቢያት፣እርሱን የሚፈሩት በመሆናቸው አወድሷቸዋል ፦

(إِنَّهُمۡ كَانُواْ يُسَٰرِعُونَ فِي ٱلۡخَيۡرَٰتِ وَيَدۡعُونَنَا رَغَبٗا وَرَهَبٗا)

‹‹እነሱ በበጎ ሥራዎች የሚቻኮሉ፣ከጃዮችና ፈሪዎች ኾነው የሚለምኑንም፣ነበሩ፤ለኛ ተዋራጆችም ነበሩ፤››

[አልአንቢያ፡90]

መላእክትም ጭምር ጌታቸውን ይፈራሉ። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(يَخَافُونَ رَبَّهُم مِّن فَوۡقِهِمۡ وَيَفۡعَلُونَ مَا يُؤۡمَرُونَ۩ ٥٠)

‹‹ጌታቸውን ከበላያቸው ሲኾን ይፈሩታል፤የታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ።››

[አልነሕል፡50]

6-

የአላህንﷻ ውዴታ ማግኘት። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

(رَّضِيَ ٱللَّهُ عَنۡهُمۡ وَرَضُواْ عَنۡهُۚ ذَٰلِكَ لِمَنۡ خَشِيَ رَبَّهُۥ ٨)

‹‹አላህ ከነሱ ወደደ፤ከርሱም ወደዱ፤ይህ ጌታውን ለፈራ ሰው ነው።››

[አልበይናህ፡8]

አላህንﷻ የሚያውቁ ትጉሃን አገልጋዮች ፍርሃት

አላህንﷻ ከሌሎች ይበልጥ የሚያውቁ ትጉሃን አገልጋዮች፣ካላቸው በጎ ሥራና ጥልቅ ተስፋ (ረጃእ) ጋር ከማንም በላይ አብዝተው ይፈሩታል። ይህን ከሚያሳዩ ምሳሌዎች የሚከተሉትን እናገኛለን ፦

-

ነቢዩﷺ ቆመው በመስገድ ላይ እያሉ፣ከተከበረው ደረታቸው ውስጥ ከማልቀስ ብዛት የድስት መንተክተክን የሚመስል ድምጽ እስኪሰማ ድረስ ማልቀሳቸው። (በአሕመድ፣በአቡ ዳውድና በነሳኢ የተዘገበ)

-

አቡ በክር  ምላሳቸውን ይዘው እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ይህ ነው ለአደጋ ያጋለጠኝ››

በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ምነው የሚበላ ዛፍ በሆንኩ ኖሮ!››

ዑመር ብን አልኸጧብም  እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ምነው ምንም የማይወሳ ነገር በሆንኩ ኖሮ! ምነው እናቴ ባልወለደችኝ ኖሮ!››

በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹አንድ አህያ በኤፍራጠስ ወንዝ ዳርቻ በርሃብ ቢሞት፣በትንሣኤ ቀን አላህ በዚያ (በመራቡ) እንዳይጠይቀኝ እፈራለሁ።››

በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹እናንተ ሰዎች ሆይ! ሁላችሁም ከአንድ ሰው በስተቀር ወደ ጀነት ገቢዎች ናችሁ ተብሎ በሰማይ ጠሪ ቢያውጅ፣እኔ ያ ሰው እንዳልሆን በእርግጥ እፈራለሁ።››

ዑሥማን ብን ዐፍፋን  እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹ከሞትኩ በኋላ ዳግም ባልቀሰቀስ እወድ ነበር።››

ሌሊቱን ሙሉ በአላህ ውዳሴ፣በሶላትና በቁርኣን ንባብ ያሳልፉ የነበሩ ሰው ናቸው እንዲህ ያሉት።

እመ ምእመናን ዓእሻ (ረ.ዐ) የሚከተለውን የአላህ ቃል ፦

(فَمَنَّ ٱللَّهُ عَلَيۡنَا وَوَقَىٰنَا عَذَابَ ٱلسَّمُومِ ٢٧)

‹‹አላህም በኛ ላይ ለገሰ፤የመርዛም እሳት ቅጣትንም ጠበቀን።››

[አልጡር፡27]

ሶላታቸው ውስጥ ያነቡና ሳያቋርጡ ያለቅሱ ነበር . . ።

(إِن تُعَذِّبۡهُمۡ فَإِنَّهُمۡ عِبَادُكَۖ وَإِن تَغۡفِرۡ لَهُمۡ فَإِنَّكَ أَنتَ ٱلۡعَزِيزُ ٱلۡحَكِيمُ ١١٨)

‹‹ብትቀጣቸው እነሱ ባሮችህ ናቸው፤ለነርሱ ብትምርም አንተ አሸናፊው ጥበበኛው ነህ (ይላል)።››

[አልማኢዳህ፡118]

አላህን መፍራት (ኸውፍን) የሚመለከቱ ብያኔዎችና ማሳሰቢያዎች ፦

1-

ስጋት (ኸሽያህ) ከፍርሃት (ኸውፍ) የጠለቀና ለየት ያለ ነው። ስጋት አላህን ይበልጥ ለሚያውቁ ትጉሃን አገልጋዮች ነው ፦

إِنَّمَا يَخۡشَى ٱللَّهَ مِنۡ عِبَادِهِ ٱلۡعُلَمَٰٓؤُاْۗ إِنَّ ٱللَّهَ عَزِيزٌ غَفُورٌ ٢٨)

‹‹አላህን ከባሮቹ ውስጥ የሚፈሩት፣ዐዋቂዎቹ ብቻ ናቸው፤አላህ አሸናፊ መሓሪ ነው።››

[ፋጢር፡28]

ፍርሃታቸው እርሱን ከማወቅ ጋር የተቆራኘ ፍርሃት ነው። ነቢዩﷺ እንዲህ ብለዋል ፦

‹‹በአላህ እምላለሁ፣እኔ ከሁላችሁም ይበልጥ እርሱን ’ምፈራና እርሱን ’ምሰጋ ነኝ።››

(በሙስሊም የተዘገበ)

ለርሱ የሚኖረን ፍርሃትና ስጋት አላህን፣ስሞቹን፣ባሕርያቱን፣ምሉእነቱን፣ግርማ ሞገሱንና ኃልልነቱን አስመልክቶ በሚኖረን ዕውቀትና ግንዛቤ ደረጃ ነው።

2-

ፍርሃት ለጥረት ለበጎ ሥራ፣ኃጢአትን እርግፍ አድርጎ በመተው ተጸጽቶ ተውበት ለማድረግ የሚያነሳሳ ሲሆን ጠቃሚ ይሆናል። ፍርሃት የሚመነጨው የኃጢአትን አስቀያሚነት ከማወቅ፣የተላለፈውን ማስጠንቀቂያ እውነተኛነት ከማረጋገጥ፣ኃያሉን ቻይ አምላክ ከማወቅ ነው። ለሰናይ ተግባር ለጥረት፣ለትጋትና ለተውበት የማያበረታታ የአላህ ፍርሃት የሚታሰብ አይደለም።

3-

አላህንﷻ መፍራት ከግዴታዎች አንዱ ሲሆን፣ለኢማን መገኘት ካለባቸው ነገሮች ውስጥም አንዱ ነው። ወደ አላህﷻ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ክቡር ከሆኑ ምዕራፎችም አንደኛውና ለልብ እጅግ ጠቃሚው ምዕራፍ ነው። በሁሉም ሰው ላይ ግዴታ (ዋጅብ) ሲሆን፣ከኃጢአቶች፣ከዱንያ፣ከመጥፎ ጓደኞች፣ከዝንጋታ፣ከቸልታና ከሕሊና ዝገት ይከላከላል።

(إِنَّمَا يَخۡشَى ٱللَّهَ مِنۡ عِبَادِهِ ٱلۡعُلَمَٰٓؤُاْۗ إِنَّ ٱللَّهَ عَزِيزٌ غَفُورٌ ٢٨) [فاطر: 28]

‹‹አላህን ከባሮቹ ውስጥ የሚፈሩት፣ዐዋቂዎቹ ብቻ ናቸው፤አላህ አሸናፊ መሓሪ ነው።›› [ፋጢር፡28]

አላህን የፈራ ሰው፣ማንም አይጎዳውም፤ከርሱ በስተቀር ሌለውን የፈራ ሰውን ማንም አይጠቅመውም።

ፈዲል ብን ዕያድ

መልመጃ

1- ለአላህﷻ ያለህን ፍራቻ የሚጨምሩ ነገሮችን ጥቀሳቸው፣በቁጥር አስቀምጣቸው።

2- የርሱን ፍራቻ የሚያመጡና የምታውቃቸውን የአላህንﷻ ስሞችና ባሕርያት ጥቀስ።

3- አላህን የሚፈራ ሰው ምን ማድረግ ይገባዋል?

ሁለተኛው ምድብ - በተግባራትና በስነምግባር ላይ የሚኖረው ዕባዳዊ አሻራዎች ፦

የአላህ ተውሒድ በሰው ስነምግባርና በድርጊቶቹ ውስጥ፣እንዲሁም በልቦናውና በጥንቁቅነቱ ላይም ይንጸባረቃል። በበግላዊ ስነምግባሩና ከሌሎች ጋር በሚኖረው ማህበራዊ ስነምግባሩ ውስጥም ይንጸባረቃል። ሕይወት በጥቅሉ ከኢማን፣ከተውሒድና ከዕባዳ መገለጫ አሻራዎች አንዱ ነው። አላህﷻ እንዲህ ብሏል ፦

( وَمَا خَلَقۡتُ ٱلۡجِنَّ وَٱلۡإِنسَ إِلَّا لِيَعۡبُدُونِ ٥٦ )

‹‹ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም።››

[አልዛሪያት፡56]



Tags: